የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች ታሪካዊ ፋይዳ
የኢትዮጵያ
ቤተ ክርስቲያንን ልዩ ከሚያደርጓት ጠባያቷ አንዱ የሀገሪቱ የታሪክ ማኅደር መሆንዋ ነው፡፡ በአፍሪካ ታሪክ ላይ
ጥናት ያደረጉ ምሁራን ከሚስማሙባቸው ነጥቦች አንዱ የአፍሪካ ታሪክ እና ቅርስ በሚገባ ተጠብቆ እንዳይቆይ ካደረጉት
ነገሮች አንዱ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ወስዶ የሚጠብቅ ሀገራዊ ማዕከል ባለመኖሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእምነት ሕግጋቷ
የምትቀበላቸውን ብቻ ሳይሆን የማትቀበላቸውን ድርሳናት እና ቅርሶች ጭምር ለትውልድ አቆይታለች፡፡ በመርጦ ለማርያም
የሚገኘው «የግራኝ አሕመድ ካባ»፣ ከሕንድ ወደ ግእዝ የተተረጎመው የሕንዶች የእምነት እና የፍልስፍና መጽሐፍ
«መጽሐፈ በርለዓም»፣ የአሪስቶትልን፣ የፕሉቶን እና የሶቅራጥስን ፍልስፍና የያዘው «አንጋረ ፈላስፋ»፣ ግብጽ
እንዴት በዓረቦች እንደ ተወረረች የሚገልጠው «የአንድ አባት ዘገባ»፣ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለዚህም
ነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ የማይሆነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት እና
ሥርዓት የማይስማሙ ወገኖች እንኳን በሀገሪቱ ጥቅሞች እና ክብሮች ላይ እስከ ተስማሙ ድረስ እነዚሀን ቅርሶች
የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው የሚባለው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን ባሕል እና ታሪክ ለትውልድ ካቆየችባቸው መንገዶች አንዱ ሥዕሎቿ ናቸው፡፡ በዚያ ፎቶ ግራፍ እና ፊልም ባልነበረበት ዘመን የነበረውን ባሕል፣ሥርዓት እና ታሪካዊ ሁነቶች የምናገኘው በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እና ግድግዳ ላይ በሚገኙ ሥዕሎች ነው፡፡
ለምሳሌ በሆሎታ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን
ግድግዳ ላይ የሚገኙት እና ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ሥዕላት ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ 44 ኪሎ
ሜትር በሆሎታ ከተማ የምትገኘው ይህች ቤተ ክርስቲያን በዐፄ ምኒሊክ አማካኝነት በ1895 ዓም የተገነባች ሲሆን
ታቦቷ የገባችው በዚሁ ዓመት የካቲት 16 ቀን ነው፡፡ ሥዕሉን የሳሉት አለቃ ሐዲስ መሆናቸውን ከመቅደሱ ምሥራቃዊ
ግድግዳ ላይ ከሣሉት ሥዕል ላይ «ለዛቲ ሥዕል እንተ ሰዓላ አለቃ ሐዲስ እም ቤተ ሌዊ፣ ወዘተምህረ በጎንደር»
በሚለው ማስታወሻቸው ይታወቃል፡፡
ሰዓሊው
የቤተ ክህነቱን እና የቤተ መንግሥቱን ወግ እና ሥርዓት በሚገባ የሚያውቁ መሆናቸውን በአሣሣላቸው ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ ወለተ ሄሮድያዳን ሲሥሏት አለባበሷን እና የፀጉር አቆራረጧን ኢትዮጵያዊ አድርገውታል፡፡ ሹሩባ
ተሠርታለች፣ነጭ ሻሽ አሥራለች፣ አሸንክታብ ሠትራ እስክስታውን ታስነካዋለች፡፡ የሄሮድስን የቤተ መንግሥት ሥርዓት
ሲስሉት በምኒሊክ ቤተ መንግሥት ሥርዓት መሠረት ነው፡፡ ይህም በዘመኑ የነበረውን የቤተ መንግሥት ወግ እንደ
ዶክመንታሪ ፊልም ለታሪክ ያስቀሩበት ሥዕል ነው፡፡ ብርሌው፣ቢላዋው፣የእንጀራው አጣጣል፣ሙዳ ሥጋው የዘመኑን የግብር
ሥርዓት በሚገባ ነው የሚያሳየው፡፡
በዚሁ የግድግዳ ሥዕላቸው ዐፄ ምኒሊክን፣ ልጅ ኢያሱን፣ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን፣ እቴጌ ጣይቱን ሥሎ አቆይቶናል፡፡
አለቃ
ሐዲስ የአድዋን ጦርነት ሂደትም በሥዕላቸው አስቀርተውልን ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ታድያ ጣልያን ኢትዮጵያን
በያዘበት ጊዜ በ1929 ዓም የሥዕሉን ሁኔታ ሰማ፡፡ የአካባቢው የጣልያን ገዥዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው
ሥዕሉን ልጠው ወሰዱት፡፡ በምትኩም «ቡዜቶ ዳንቴ» በሚባል ሰዓሊ ማንነቱ የማይታወቅ የአንድ ሰው ሥዕልና ፣የቅዱስ
ጊዮርጊስን ሥዕል በጣልያን ባህል መሠረት አስሳሉበት፡፡ ይህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ሥዕሎች ታሪካዊ
ፋይዳ የሚያመለክትና በሀገሪቱ ላይ የሚመጡ ታሪካዊ ጠላቶች ሁሉ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸውን አመለካከት
ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ
ውስጥ አንድ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ ማለት «ጣራ እና ግድግዳ ያለው የማምለኪያ ቦታ ተቃጠለ» ማለት ብቻ
አይደለም፡፡ «የኢትዮጵያ አንዱ አካሏ፣ ምናልባትም ዋናው አካሏ ተቃጠለ» ማለት ጭምር ነው፡፡ «ኢትዮጵያ ውስጥ
የአንድ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ፈረሰ፣ተበላሸ፣ውኃ ገባበት፣ተሰነጠቀ ማለት የአንድ ሺ ዓመት ታሪካዊ ድርሳን ላይተካ
ወደመ» ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ ማለት «ጣራ እና ግድግዳ ያለው የማምለኪያ ቦታ ተቃጠለ» ማለት ብቻ አይደለም፡፡ «የኢትዮጵያ አንዱ አካሏ፣ ምናልባትም ዋናው አካሏ ተቃጠለ» ማለት ጭምር ነው፡፡ «ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ፈረሰ፣ተበላሸ፣ውኃ ገባበት፣ተሰነጠቀ ማለት የአንድ ሺ ዓመት ታሪካዊ ድርሳን ላይተካ ወደመ» ማለት ነው፡፡
ReplyDeleteበጣም ነው የሚማርከው
ReplyDelete